የጀዋርን ሩብ አትሆኑም!
-----
ስለኢትዮጵያ ፖለቲካ ማውራት እጅ እጅ ብሎናል። ነገር ግን በቆሎ-ጆሌ ንግድ የከሰሩ አቅል አልባዎች እየነካኩ ያናግሩናል።
-----
ጀዋር ሙሐመድ የሰው ልጅ ነው። የሰው ልጅ በሚሰራው ስራ ሊሳሳት ይችላል። በመሆኑም ጀዋር ሲሳሳት "ተሳሳትክ" ማለት ያለ ነገር ነው። እኛም ስሕተት መስሎ የተሰማንን ሁሉ ስንነግረው ነበር።
ጀዋር ከእስር ተፈትቶ "ኡቡንቱ" ከተባለ የዩቲዩብ ሚዲያ ጋር ቃለ-ምልልስ ካደረገ ጀምሮ በእርሱ ላይ የሚካሄደው ዘመቻ ግን ስህተትን መጠቆም እና ትችትን መግለጽ ሳይሆን በጥላቻ ዘመቻ ህዝቡን አደናግሮ ልጁን ከህዝብ ጋር የማራራቅ ተንኮል ነው።
-----
አንድ ነገር ልንገራችሁ!!
ይህ ዘመን በቲፎዞ ብዛት ህዝብን እያምታቱ ደጋፊን የሚያበራክቱበት ነው። ብቃት እና ችሎታ የሌለው ሙስኬቶ ሁላ ጀግና መስሎ የሚንጎማለለው በአብዛኛው በሰራው ስራ ሳይሆን በቲፎዞ ወከባ ነው። ዛሬ በሚዲያ እየቀረቡ ጀግና መስለው ከሚደነፉብን የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችና ተንታኞች ነን ባዮች መካከል 90% የሚሆኑት populism በሚባለው የሆሊጋኖች ማምታቻ ዘዴ እየተስፈነጠሩ ወደ ላይ የወጡ ናቸው።
ጀዋር ሙሐመድ ግን ከእነርሱ ይለያል። አንደኛ፣ ተጨባጭና ውጤታማ የሆነ ስራ ሰርቷል። በኢትዮጵያ ታሪክ የእርሱን ያህል ተጽእኖ መፍጠር የቻሉ ግለሰቦች የታዩት በጥቂት ወቅቶች ነው። ጀዋር አንድ ግለሰብ ሆኖ በአራት ዓመት ውስጥ ብቻ በርካታ ድርጅቶች ያልሰሩትን ነገር ሰርቷል። በተለይ ግን ምድረ ኮልኮሌውን ሁሉ እርሱ በሚጠራበት ስም "activist" እያሉ መጥራት ያሳፍራል።
ሁለተኛ፣ ጀዋር ለመሪነት፣ ለፖለቲከኛነትም ሆነ ለተንታኝነት ብቁ ነው። ለጸሐፊነትም ብቁ ነው። በሶስት ቋንቋዎች ፍሱሕ ሆኖ መናገር ይችላል። እውቀቱ በጣም ሰፊ ነው። ስለፖለቲካ ሳይንስ ብቻ ሳይሆን ስለሌሎች ፊልዶችም ብዙ አንብቧል። ከበርካታ የታሪክ አውራዎቻችን ጋር እየተገናኘ የአንደኛ ደረጃ መረጃዎችን ሰብስቧል።
እርግጥ ጀዋር በአሁኑ ጊዜ ባላወቅነው ምክንያት ዝም ብሏል። ቢሆንም ዝም ማለት መብቱ ነው። ስለዚህ ተናገር ብለን አንጎተጉተውም። ያለፈውን ገድሉን እያስታወስን ዛሬም እናከብረዋለን። ዛሬም እናሞግሰዋለን።
-----
ጀዋርን የሚዘልፉት!
ስለእነርሱ ለመናገር እና ለመጻፍ አፍራለሁ። ነገር ግን በፖለቲካው ረገድ ሁላቸውም ቢደመሩ የጀዋርን የሩብ ሩብ አይሆኑም።
ዛሬ ጀዋርን ለማንጓጠጥና ለመዝለፍ አፋቸውን ያሞጠሞጡት ዋልጌዎች እና ምንደኞች ሚዛን የማይደፉ አሜኬላዎች መሆናቸው የተጋለጠው ጀዋር ታስሮ በቆየበት ወቅት ነው። በዚያ ወቅት ምን የሰሩት ነገር አለ? የወያኔ ኮርቻ መሆናቸውን ከማሳየት ውጪ አንድም ቁም ነገር አልሰሩም።
-----
አፈንዲ እና ጀዋር
እዚህ ኢንተርኔት ላይ ከሚወዛገበው ጀማ በፊት ነው ጀዋርን የማውቀው። ከሁልሽም በፊት ነው የምናውቀው። እኔ የተወለድኩበት ገለምሶ (ሀረርጌ) እና እርሱ የተወለደባት ዱሙጋ (አርሲ) 65 ኪሎሜትር ብቻ ነው የሚራራቁት። በዕድሜ በአምስት ዓመት ያህል ብበልጠውም የአንድ ዘመን ሰዎች ነን።
ብዙዎች እንደሚያስቡት ታዲያ እኔ እና ጀዋር በአመለካከታችን 100% ተመሳሳይ አይደለንም። በመካከላችን ብዙ ልዩነቶች አሉ (እኔ "ኤርትራዊ" መሆኔንም አስታውሱ)። ነገር ግን የሚያቀራርበን ነገር ይበልጣል። ልዩነት ማለት ደግሞ ጠላትነት አይደለም። ደግሞ ሳትደርስበት የሚደርስብህና ስምህን እያጠፋ ነገር የሚፈልግህ ሰው ጠላት ብቻ ሳይሆን "ጭቶ ሚልኪ" ነው።
-----
አፈንዲ ሙተቂ
መስከረም 9/2015
0 Comments