ጥቅምት 24፡ መቼም አንረሳውም!
ጥቁሩ ቀን 2ኛ አመቱ ተቃርቧል። ሀገር እንጠብቅ ህዝብን እናገልግል ያሉ፣ ቀን ገበሬ ማታ ደግሞ ጠባቂ ሆነው ለሃያ አመታት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የኖሩ፣ ሃሩሩ አቃጠለኝ በቃኝ፣ ብርዱ አቆረፈደኝ ይቅርብኝ ሳይሉ፣ ሌትና ቀን፣ በጋና ክረምት፣ ቆላና ደጋ እያሉ ስለሀገር መስዋዕትነት የከፈሉ፣ ስለህዝብ የተንገላቱ፣ ስለኢትዮጵያ የደከሙ የሰሜን እዝ አባላት በሰው ልጅ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ባልጠበቁት አካል፣ ባልጠረጠሩት መንገድ፣ ባልገመቱት ሰዓት እንኳን ለወንድም፣ እንኳን ለአንድ ሀገር ልጅ ለጠላት እንኳን በሚሰቀጥጥ መልኩ የተጨፈጨፉበት ሁለተኛ አመት ነው! ጥቅምት 24።
ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ ጥቁር ቀን ነው፣ ይህ ቀን ኢትዮጵያውያን በሙሉ ያነቡበት ቀን ቀን፣ ይህ ቀን ምስኪን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን በተኙነት የታረዱበት ቀን ነው፣ ይህ ቀን የታሪክ ጠባሳው ለዘላለም የሚኖር ቀን ነው። ይህንን ቀን ስናስታውስ በተኙበት የታረዱት ሀገር ጠባቂዎች፣ አስክሬናቸው ላይ በሲኖትራክ በጭካኔ የተነዳባቸው ወታደሮች፣ የሀገሬ ልጅ ያሉት ሲጨክንባቸው እራቁታቸውን ወደ ጎረቤት ሀገር ያመለጡ የሰራዊቱ አባላት የሚታወሱበት ቀን ነው።
ዛሬ ላይ የነርሱ መስዋዕትነት ሀገርን አቅንቷል፣ የከፈሉት ዋጋ ለተቀረነው ለኛ የታሪክ ባላደራ እንድንሆን አድርጎናል። ሀገር እንድትቀጥል እነሱ ምክንያት ሆነዋል።
ዛሬ መላ ኢትዮጵያዊ ወገኖቼን ቆሜ አንድ ነገር እጠይቃችኋለው። ከዛሬ በኋላ እስከ ጥቅምት 24 ያሉትን አምስት ቀናት በዛ ጥቁር ጭለማ ቀን ሰብል ሲሰበስቡ ውለው በውድቅት ሌሊት የተጨፈጨፉትን ውድ ልጆቻችንን እንድናስታውስ አደራ እላለሁ። ውድ ኢትዮጵያውያን የነርሱ መስዋዕትነት ዛሬ ለኛ የመኖር ዋስትና መቀጠል ምክንያት ሆኗልና ከዛሬ ጀምሮ ያሉትን 5 ቀናት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በምናደርገው እንቅስቃሴ መስዋዕትነታቸውን የሚያክብርና የሚዘክር እንዲሆን አደራ እልችኋለው። በመሆኑም ጥቅምት 24 2013ን እያስታወስን አንድ ነገር በማድረግ መስዋዕቶችን እናስብ!
ሁላችንም የጥቅምት 24 መስዋዕቶችን የሚያስታውስ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ ገፃችን ላይ (Profile Picture) ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥቅምት ማለቂያ ድረስ በማድረግ በአንድነት በመቆም ለጥቅምት 24 የጭፍጨፋ ሰለባዎች፣ ከጭፍጨፋው ተርፈው ሀገርን ለማቅናት በዱር በገደል አሁንም እየተዋደቁ ለሚገኙ ጀግናና ብርቅ ልጆቻችን ድጋፋችንን እንድናሳይ በትህትና እጠይቃለሁ።
የሰሜን እዝ መስዋዕትነት ይሰማኛል የሚል ማንም ኢትዮጵያዊና የኢትዮጵያ ወዳጅ ይህንን መልዕክት ወይንም መሰል መልዕክቶችን በማሰራጨት እንቅስቃሴውን ይቀላቀል።
ጥቅምት 24፡ መቼም አንረሳውም
መስዋዕትነታችሁ አገርን አቁሟል፤
ሱሌማን አብደላ
0 Comments