ወንድም ሙአመር ጋዳፊ- ትንግርተኛው መሪ(Muhammad Gadafi

-----
ጸሐፊ: አፈንዲ ሙተቂ
-----
የሊቢያ ዐረብ ጀምሃሪያ አብዮታዊ መሪ የነበሩት ወንድም ሙአመር አል-ቀዟፊ (ጋዳፊ) ከሞቱ ከነገ ወዲያ (ጥቅምት 11/20015) አስራ አንድ ዓመት ይሞላቸዋል፡፡ እኝህ ሰው ከመሞታቸው በፊት ትንቢት በሚመስል መልኩ እንዲህ ብለው ነበር ይባላል።

"ውድ የሊቢያ ህዝብ! በአሁኑ ወቅት ሀገራችሁን በዘዴ ማስተዳደር የሚችል እንደኔ ያለ መሪ አታገኙም። እናንተም የበደልኩት ነገር የለም። ስለዚህ ተቃውሞአችሁን ተውትና እንነጋገር። የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲቀሰቀስ መንገድ አትክፈቱ"

እነሆ በእርሳቸው ዘመን "የበረሃ ገነት" ትባል የነበረችው ሊቢያ እርሳቸው ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ሀገር መሆን አልቻለችም። ዛሬም የደም ጎርፍ እየፈሰሰባት ነው።

እርግጥ ጋዳፊ በእርሳቸው ላይ የተነሳውን ተቃውሞ የያዙበት መንገድ አግባብ አልነበረም። እንደ ሞሮኮ እና እንደ ኦማን መንግሥታት ለህዝቡ ተጨማሪ incentive ሰጥተው ተቃውሞውን ማብረድ ይችሉ ነበር። ሆኖም ተቃውሞውን በሃይል ለመጨፍለቅ ሞክረው የNATOን ጦር በራሳቸው ላይ መጋበዛቸው እርሳቸውንና ሀገራቸውን ትልቅ ዋጋ አስከፍሎአቸዋል።

ጋዳፊ በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት አምባገነን መሆናቸው ባይካድም ለህዝባቸው ብዙ መልካም ነገሮችንም ሰርተዋል። እኝህ ሰው በዓለም ህዝቦች ዘንድ በጣም የሚታወሱት ግን ይሰሯቸው በነበሩት የተለያዩ ትንግርቶች ነው። በዚህ ጽሑፍ ከጋዳፊ ትንግርተኛ ድርጊቶች መካከል የተወሰኑትን እንጋራለን፡፡
*****
ሊቢያ በጋዳፊ ዘመን በብዙ ሀገራት ኤምባሲዎችን ከፍታለች፡፡ ታዲያ በወንድም ጋዳፊ አብዮታዊ እይታ መሰረት “ኤምባሲ” የሚለው ቃል የአድሃሪያንን የፖለቲካ አሻጥርና ውንብድና የሚወክል ቃል በመሆኑ አብዮታዊያን ሊጠቀሙበት አይገባም፡፡ በተለይ ይህ የኢምፔሪያሊስቶችን ፍላጎት የሚገልጽ ቃል ለሊቢያ አይመጥናትም፡፡ ስለዚህ ወንድም ጋዳፊ በየሀገሩ የተከፈቱትን የሊቢያ ኤምባሲዎች “የታላቋ ሶሻሊስት ሊቢያ ዐረብ ጀመሃሪያ ህዝባዊ ጽሕፈት ቤት” በሚል ስም እንዲጠሩ አድርገዋል፡፡
*****
“የታላቋ ሶሻሊስት ሊቢያ ዐረብ ጀማሀሪያ” መሪ የነበሩት ወንድም ሙአመር አል-ቀዛፊ (ጋዳፊ) በየሀገሩ ጉብኝት በሚያደርጉበት ወቅት የሚከተሉት ፕሮቶኮል ከታላቋ ሊቢያ ጋር የሚመጣጠን መሆን ይገባዋል የሚል እምነት ነበራቸው፡፡ በመሆኑም በጉብኝታቸው ወቅት በርካታ አጃቢዎች ይከተሏቸዋል፡፡ የወታደር ጠባቂዎቻቸውም ብዙ ናቸው፡፡ ከነርሱም መካከል አስራ አምስቱ ሴት ኮማንዲስቶች ናቸው፡፡

እነዚያ ኮማንዲስት ሴቶች ጋዳፊ ለቤተ መንግሥታቸው ክብር ካሰናዱት ልዩ ብርጌድ የተውጣጡ ናቸው፡፡ የዚያ ብርጌድ አባላት በሙሉ ልጃገረዶች ሲሆኑ እያንዳንዷ ልጃገረድ ከወንዶቹ በእጥፍ የሚበልጥ ደመወዝ ይከፈላታል፤ ያማረ ቪላም ይሰራላታል፡፡ ታዲያ ልጅቷ ምንጊዜም ቢሆን ድንግልናዋን መጠበቅ ይገባታል፡፡ ድንግልናዋን ከሸጠችው ግን ሁሉንም ጥቅማጥቅም ታጣለች፤ ከሰራዊቱም ትባረራለች፡፡ ይሁንና በዚህ ሁኔታ የተባረረች ሴት አልነበረችም፡፡ ሁሉም ሴቶች ጋዳፊ ስልጣናቸውን እስኪያጡ ድረስ ድንግሎች ነበሩ (እኛ ውስጡን አናውቅም። የሚባለውንና የሚጻፈውን ነው የነገርናችሁ)፡፡
*****
ጋዳፊ የዝነኛው “አረንጓዴው መጽሐፍ” ደራሲም ናቸው፡፡ መጽሐፉ በሶስተኛው ዓለም የሚመሰረት አብዮታዊ መንግሥት ምን መልክ ሊኖረው እንደሚገባ እና ምን ዓይነት ስራዎችን መስራት እንዳለበት ይተነትናል፡፡

  አንድ ጊዜ ታዲያ የደርግ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት በዓለም ሀገራት እየዞሩ ስለሚያዋቅሩት መንግሥትና ስለመጻኢ እቅዳቸው ማብራሪያ ይሰጡ ነበር፡፡ እነዚሁ ባለስልጣናት ወደ ሊቢያ ጎራ በማለት ስለተልዕኮአቸው መግለጫ ሲሰጡ ጋዳፊ ተገርመው “እኛን ሳታማክሩ አብዮት ማካሄዳችሁ ትክክል አይደለም፤ ለወደፊቱ ለልምድ እንዲጠቅማችሁ አረንጓዴውን መጽሐፍ ማንበብ አለባችሁ” በማለት መጽሐፋቸውን ለባለስልጣናቱ አድለዋል፡፡
*****
  በሌላ ጊዜ ደግሞ ጓድ መንግሥቱ ኃይለማሪያም ሊቢያን ይጎበኛሉ፡፡ መንጌ በጉብኝቱ ማብቂያ ለክብራቸው በተዘጋጀው የእራት ግብዣ ላይ ያዩትን ነገር እንዲህ ተርከውታል፡፡

   “ግብዣው የተዘጋጀው በድንኳን ውስጥ ነው፤ አስተናጋጆቹ እራቱን ወደኛ በሚያመጡበት ጊዜ ያየሁትን ማመን አቃተኝ፤ እነዚያ አስተናጆች ነጮች ሲሆኑ እራቱን እንደያዙ በእንብርክካቸው ይሄዱ ነበር፤ ጋዳፊ አስተናጋጆቹ እንደዚያ እንዲሄዱ ያደረገው አፍሪቃዊያን ነጮችን ማንበርከክ ይችላሉ ከሚል እምነቱ ተነስቶ ነው፤ ሆኖም አስተናጋጆቹ በእምብርክክ በመሄዳቸው ብዙ ብር ተከፍሎአቸዋል”
*****
ጋዳፊ በጣም አስደማሚ ትንግርት የፈጸሙት በቶጎ ሀገር ነው፡፡ አንድ ጊዜ በዚያች ሀገር የአፍሪቃ መሪዎች ስብሰባ ሲደረግ ጋዳፊ ስብሰባው ይሰለቻቸውና ጠባቂዎቻቸውን ይዘው ገጠሩን ለመጎብኘት ይወጣሉ፡፡ በሽርሽራቸው ወቅት አንዲት ደሃ አፍሪቃዊት እንጨት ተሸክማ ወደ ቤቷ ስትሄድ ያገኟታል፡፡ ሴትዮዋ በአጀብ የሚሄዱትን ጋዳፊ ስታይ ቆም ብላ በፈገግታ ታስተውላቸው ጀመር፡፡

  ጋዳፊም ወደ ሴትዮ ቀረብ በማለት “አንቺ ሴት! እኔ ማን እንደሆንኩ ታውቂያለሽ?” በማለት ይጠይቋታል፡፡ ሴትዮዋም “በርግጥ ማን እንደሆኑ አላውቅም፤ እንዲሁ ሳይዎት ግን ደግ ሰው ይመስሉኛል” የሚል መልስ ትሰጣለች፡፡ ጋዳፊም ወደ አጃቢዎቻቸው ዞር ብለው “እዚያ ስብሰባ ላይ የአፍሪቃ መሪዎች ከሚያሳዩኝ የውሸት ፈገግታ ይልቅ የዚህች ደሃ ሴትዮ ፈገግታ ይበልጣል” አሏቸው፡፡ በማስከተልም በቶጎ ዋና ከተማ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል አሰርተው ቁልፉን ለሴትዮዋ አስረከቧት፡፡ ያቺ ሴት ዛሬ ከቶጎ ታዋቂ ሀብታሞች አንዷ ሆናለች፡፡
*****
እኚህ ወንድም ጋዳፊ የአግራሞት ምንጭ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በበርካታ ጉዳዮች ከብዙ የአፍሪቃ መሪዎች ይቀድሙ ነበር፡፡ ለምሳሌ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪቃ ህብረት የተሸጋገረው በእርሳቸው አንቀሳቃሽነት ነው (የህብረቱን ጽ/ቤት ወደ ሊቢያ ለመውሰድ ያካሄዱት ዘመቻ ቢያናድደንም አዎንታዊ ጎናቸው ሊጠቀስ ይገባል)፡፡ ለአፍሪቃ ህብረት ከፍተኛ መዋጮ የሚከፍሉትም እርሳቸው ነበሩ፡፡ የጋዳፊዋ ሊቢያ ከአፍሪቃ ህብረት በጀት ግማሽ ያህሉን ትሸፍን ነበር።

የደቡብ አፍሪቃ ጥቁሮች፣ የናሚቢያ ሸማቂዎች፣ በሙጋቤ የሚመሩት የዚምባብዌ አርበኞች፣ የምዕራብ ሳሓራው ፖሊሳሪዮ ለነጻነት ያደረጉትን ትግል በገንዘብና በመሳሪያ በመደገፍም አንደኛ ነበሩ፡፡ በበርካታ የአፍሪቃ ሀገራት መካከል የተከሰቱ ግጭቶችንም በሽምግልና ለመፍታት ጥረት አድርገዋል፡፡

ጋዳፊ ለፍስልጥኤማዊያን ያሳዩት የነበረው ድጋፍ ወደር የለሽ ነበር። የፍልስጥኤም አስተዳደር በእርሳቸው ባገኘው የፋይናንስ ድጋፍ  ብዙ ፕሮጀክቶችን አከናውኗል። በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ጀምሮ በዚያን ጊዜ የሶሻሊስት ስርዓት ይከተሉ በነበሩት የአፍሪቃ ሀገራት ሁሉ በሊቢያ ድጋፍ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ነበሩ (ለምሳሌ በሀገራችን ተጀምሮ የነበረው "የኦሞ ሸለቆ ፕሮጀክት" የፋይናንስ ምንጩ ከሊቢያ ነው)።

እዚህ ላይ ታዲያ ወንድም ሙአመር ቀዟፊ (ጋዳፊ) ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር የተጋቡትን እልህ ሳንጠቅስ ብናልፍ ዳሰሳችን ሙሉ አይሆንልንም። ጋዳፊ ከአሜሪካ ጋር እልህ የተጋቡት አሜሪካ በያኔው ቋንቋ "ኢምፔሪያሊስት" ስለሆነች እና እስራኤል በፍልስጥኤማዊያን ላይ የምትወስዳቸውን እርምጃዎችን ሁሉ ስለምትደግፍ ነበር። እስራኤል ደግሞ በአሜሪካ የቬቶ ፓወር ተመክታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች እየጣሰች ፍልስጥኤማውያን ላይ ከባድ ግፍ በማድረሷ ጋዳፊን ታበግናቸው ነበር። በመሆኑም በያሲር አረፋት ከሚመራውና ለድርድር ዝግጁ ከነበረው PLO በተጨማሪ በእስራኤልና በምዕራባዊያን ላይ የሽብር ጥቃት የሚያካሄደውን የአቡ ኒዳል ድርጅት (The Abu Nidal Organization) ይደግፉ ነበር።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬጋን በጀርመን የሰፈሩ የአሜሪካ ወታደሮች በሚዝናኑበት የናይት ክለብ ላይ የደረሰውን ፍንዳታ አሳብበው በሊቢያ ላይ የአየር ድብደባ ሲፈጽሙ ደግሞ የሊቢያ የደህንነት ተቋም አንድ የPAN-Am አየር መንገድ አውሮፕላን በስኮትላንዷ የሎከርቢ ከተማ በአየር ላይ የጋየበትን ድርጊት በማቀናበር ተበቅሏል። ይሁን እንጂ ይህ አደጋ በዝምታ አልታለፈም። የሊቢያ ደጋፊ የነበረችውን ሶቪየት ህብረትን ጨምሮ ብዙሃኑ የአለም ሀገራት አደጋው በጥልቀት እንዲመረመር ድምጻቸውን አሰምቷል። ከአደጋው ጀርባ የሊቢያ እጅ እንዳለ ሲረጋገጥ ደግሞ በሀገሪቱ ላይ ዓለም አቀፍ የበረራ ማእቀብ ተጥሏል። አሜሪካ ደግሞ ሊቢያን "ሽብርተኝነትን በገንዘብና በማቴሪያል ከሚደግፉት ሀገራት አንዷ" በማለት ፈርጃለች።

ይህ ውዝግብ የተፈታው በሁለት መንገዶች ነበር። በቅድሚያ በድርጊቱ ውስጥ እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩት "ላሚን ኽሊፋ ፈሂማ" እና "ዐብዱልባሲጥ አል-ሚግራሂ" የተባሉት የሊቢያ ዜጎች ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተደረገ። ላሚን ከሊፋ ፈሂማ እጁ ነፃ ሆኖ በመገኘቱ ከዓመት በኋላ ተለቀቀ። ዐብዱልባሲጥ አል-ሚግራሂ ግን ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት (ይህ ሰው በ1999 ታስሮ የጤና ሁኔታው በጣም በመቃወሱ በ2009 ተፈትቷል። ከእስር ከወጣ በኋላም ብዙ ሳይቆይ በ2012 ሞቷል)።

ጋዳፊ ብዙዎችን ያስደነቀ አቋም የወሰዱት ደግሞ በ2003 ነው። በዚያ ዓመት በስኮትላንድ አየር ላይ ለደረሰው የአውሮፕላን ፍንዳታ ሃላፊነቱን ወስደው ለካሳ የሚሆን የብዙ ቢሊዮን ዶላር ክፍያ ፈጽመዋል። አውሮፕላኑ እንዲጋይ እንዳላዘዙ ገልጸው ቦንቡን ያፈነዱት የራሳቸው ሠራተኞች በመሆናቸው በአደጋው የተጎዱ ቤተሰቦችን ይቅርታ ጠይቀዋል። (በነገራችን ላይ በሊቢያ ላይ የተጣለው ማእቀብ በሀገሪቱ ላይ ያደረሰው ጉዳት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በተመሳሳይ መልኩ በኢራቅ ላይ ተጥሎ የነበረው ማእቀብ ግን በሀገሪቱ ላይ ከባድ ጉዳት አድርሷል። በማእቀቡ የተጎዳው ደግሞ የኢራቅ መንግሥት ሳይሆን ህዝቡ ነው)።

ወንድም ሙአመር ጋዳፊ ሌሎች ሀገሮችን በገንዘብ ይደግፉ የነበሩት የሀገራቸውን ህዝብ ሳይዘነጉ ነው። የሊቢያ ህዝብ በእርሳቸው ዘመን ውሃ፣ ኤሌክትሪክ፣ የመኖሪያ ቤት፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ወርሃዊ ቀለብና የተለያዩ አገልግሎቶችን በነፃ ያገኝ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ለእያንዳንዱ ሊቢያዊ በነፍስ ወከፍ ሁለት መቶ ዶላር ይከፈለው ነበር። እርሳቸው ሲገደሉ ግን ሁሉም ነገር ቀረ። ሊቢያም ለኑሮ ከሚያስፈሩት የዓለም ሀገሮች አንዷ ሆነች።
-----
አፈንዲ ሙተቂ
መጀመሪያ ጥቅምት 6/2007 ተጻፈ።
እንደገና ተሻሽሎ ጥቅምት 7/2015 ተጻፈ።
----
©Afendi Muteki, October 2022
-----